ገፆች

ሐሙስ 3 ሜይ 2018

ረቂቁ አቶም (ክፍል 1ሃ) - የሁሉም ነገር መነሻ

በአስር ዓመቴና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያልሁ ነው አንዲት መጽህፍ ልመለከት የቻልኩት። ይህች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈች "ዘ ቴሌስኮፕ ኤንድ ማይክሮስኮፕ" (The Telescope and Microscope) አርስት የነበራትና ለልጆች እንዚህን መሳሪያዎች ለማስተዋወቅ ተብላ የተጻፈች ነበረች። በቀጣዩም ህይወቴ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ላለኝ ከፍተኛ ዝንባሌና አክብሮት መነሻ እቺ ትንሽ መጽሃፍ ነበረች ለማለት ያስደፍረኛል ። በከፍተኛ ደረጃ የምንመካበት ለማየት ችሎታችን ምክኒያት የሆንው ዓይን የተባለው የሰውነት ክፍላችንን ድክመት በማጋለጥ፣ ለነዚህ መሳሪያዎች ባይሆን ልናየው የማንችለው ሌላ ድብቅ ዓልም መኖሩን ተገነዘብኩ። እንደዕድሌም ሆኖ በልጅነቴ ከአባቴ ጓደኛ በስጦታ አንድ የልጆች ማይክሮስኮፕ፣ ከዚያም ሁለትኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ቤተሰቦቼን በመጭቅጭቅ ጥራት ያለው ለምርምር የሚበቃ ማይክሮስኮፕ ባለቤት ለመሆን ችዬ ነበር። እንዲሁም ከዚች መጽህፍ ካገኘሁት መረጃ ከዓይን መነጽር በተገኘ መስታወት ደከም ያለ ቴሌስኮፕ መስራት ችዬ ነበር። በተለይ በማይክሮስኮፖቹ በግቢያችንና በአካባብያችን በሚገኙ ውሃ አካሎችን በመመርመር ብዙ ሰዓታትን አሳልፍ ነበር። እግረመንገዴንም ለአቶሞች መኖር ዋነኛ ማስረጃዎች ለአንዱ ምስክር ልሆን ችያለሁ።
ወደ አርስታችን ስንመለስ አብዛኛዎቻችን ሁሉም ነገር እጅግ በጣም ረቂቅ ከመሆናቸው የተነሳ በምንም ዓይነት ማጉያ መሣሪያም ቢሆን በነጠላ ለመመልክት ምንም ተስፋ በሌለን አቶም በተባሉ አካሎች እንደተሠራ እናውቃለን ወይም እንሰማለን። ሁሉም ነገር በምድርም በሰማይም ከአቶም ነው የተሠራው ካልን በመጠኑ እነዚህን ስውር ነገሮች መረዳት ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ግለሰብ (በአቶም የተሠራ እንደመሆኑ መጠን) የስኳር ህመም አለበት ከተባለ፣ አቶሞቹ በዚህ ጉዳይ ምንድነው ሚናቸው? የአዕምሮ ህመምስ ቢሆን። የምንበላው የምንጠጣው፣ የምንጓጓዝበት፣ በርቀት የምንነጋገርብት፣ የምንለብሰው፣ የምንጠለልበት ሁሉም ከአቶም ነው የተሠራው ካልን፣ ይህን ሁሉ የመገንባትና የማቀፍ ችሎታ ያለው አቶም ምንደንው? አቶሞችን በምንም ዓይንት መመልከት የማይቻል ከሆን ለመኖራችው ምን መረጃ አለን? እነዚህን ምሰል ጥያቀዎችን ለመመለስ ወደኋላ ብለን የግኝታቸውን ታሪክ መመልከት ይኖርብናል።
የተለያዩ ጥንታዊ ህብረተሰቦች በጣም በርካታና ውስብስብ የሆኑ የሚመለከቷችውንና ይሚገለገሉባቸውን የተለያዩ ነገሮችን ሁሉ የተሰሩባቸው ነጥረ ነገሮች ብዛት ምናልባት ከማሰብ ከመረዳትና ከመቁጠር አቅማችው በላይ ሲሆኑባቸው ሳይሆን አይቀርም፣ ጉዳዩን ለማቃለል እነዚህ ሁሉ የተሠሩት ጥቂት ውስን የሆኑ ንጥረነገሮችን በተለያየ መጠን በመቀላቀል ሊሆን ይቻላል ብለው የገመቱት።
ለምሳሌ ጥንታዊ ግሪኮች ሁሉም ነገር ከአራት ብቻ ንጥረ ነገሮች የተሠሩና እነዚህም ምድር፣ አየር፣ እሳትና ውሃ ሲሆኑ፣ ከበድ ያሉት የምድሩ መጠን የበዛ ሲሆን፤ ቀለል ያሉት ደግሞ በብልጫ አየር ይይዛሉ ወዘተ… ሲሉ ለዚህም ዕምነት ምንም አይንት ግልጽ መረጃ ሳይኖራቸው በበለጠ ከፍልስፍና ከጥንቆላ ጋር ያያይዙት ነበር።
የመጀመሪያው አቶም ለመኖሩ ግልጽና አሳማኝ መረጃ የተገኘው እንደ አውርፓውያን አቆጣጠር አስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያው ላይ ጆን ዳልተን በተባለ ግለሰብ አማካይነት ሲሆን፣ እሱም አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ሲቀላቀሉ የሚፈጠረው አዲስ ነጥረ ነገር ውስጥ የሚኖራቸው ተመጣጣኝንት፣ ሁልጊዘም በአነስተኛ ቁጥር ክፍልፋይ እንደሆነ ታዘበ።
በተጨማሪም የቅልቅል ውጤቱን መልሰን ወደ መነሻ ንትረ ነገሮቹን ብንለያይ፣ የፈለግንውን ያሁል መጠን ብንሰፈር የመነሻዎቹ ክፍልፋይ አይለያይም። በጣም ትንሽ መጠን ሰፍረን አንድ እጅ ለሁለት እጅ ካገኘን፣ መካከለኛ ስንሰፍር ያንኑ አንድ እጅ ለሁለት እጅ ነው የምናገኘው። ብዙም ብንሰፍር እንደዚያው ። ለምሳሌ ክፍልፋዮቹ አንድ ለአንድ፣ አንድ ለሁለት፤ ሁለት ለሶስት፤ አንድ ለአራት ሊሆኑ ሲችሉ አ ንድ ለዘጠን፤ አምስት ለአስራሰባት፤ አስራሶስት ለመቶ ዓይነት ክፍልፋዮች ግን ሲሆኑ አይታይም። ይህን የመሰለ ውጤት ማግኘት የምንችለው ማንኛውም ነገር በማይከፋፈሉ በሙሉ ቁጥር ብቻ በሚዋህዱ ረቂቅ አካሎችን በማብዛት የተገነቡ ሲሆን ብቻ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። ሌላው ለአቶም መኖር የተግኘው መረጃ እንደ አውርፓውያን አቆጣጠር 1827 ዓም በእጽዋት ተመራማሪው ሮበርት ብራውን ሲሆን በማጉያ መነጽር ውሃ ውስጥ ያሉ የአዋራ ብናኞችን ሲመለከት ያለማቕርጥ በተለያየ አቅጣጫ ሲወርጩ ታዘበ። እኔም በለጅነቴ ለመመልከት ዕድል የነበረኝ ይህንኑ ነበር። ለዚህም ክስተት ምክኒያት ብናኞቹ በውሃው አቶሞች በመገጫጨታቸው መሆኑን ገመተ። ቆየትም ሲል በ1905 አልበርት አይንሳታይን የዚህን እንቅስቃሴ ባህርይ ሳይንሳዊ በሆነ አካሄድ አብጠርጥሮ ከተነተነ በኋላ፣ ጂን ቴሪን የተባለ ሳይንቲስት እንቅስቃሴውን በጥንቃቄ በመለካት የአቶሞችን ክብደተና ስፋት መገመት ችሏል።
በክፍል ሁለቱ ልጥፍም ስለአቶሞቹ መጠንና ዓይነት፣ እንዲሁም ስለውህደታቸውና ከሒወታችን ጋር ስላላቸው ቁርኝት አንዳንድ ነጥቦችን ለመግለጽ እሞክራለሁ።