ገፆች

ዓርብ 18 ዲሴምበር 2020

የሳይንስና የሂሳብ ቁርኝት - ስለወረርሽኝ የሚነግረን

የሂሳብ ወይም ማትማቲችስ ከሳይንስ ጋር ከፍተኛ ጥምረት እንዳለው ብዙዎቻችን አንዘነጋም። ዘመናዊ ህክምናም ሳይንስ ላይ የተመሠረት እንደመሆኑ መጠን ብስፋት የሂሳብ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ከህክምና ሳይንስ መካከል የወረርሽኝ ጥናትን ያካተተው ኤፒዴምዮሎጂ (Epidemiology) የተባለው ዘርፍን ስንመለከት ከሂሳብ ጋር ያለው ቁርኝት ከፋ ያእ ነው። ቀጥለን የዘንድሮውን የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝም አስታከን፣ ሂሳብ በምን ዓይነት ወረርሺኝን ለመረዳት እንደሚያስችለን እንመልከት።

ለመነሻም ያህል ለአንድ ቀን ብቻ ህምም የሚያስከትል ተላላፊ በሽታን እንመልከት። በተጨማሪም በዚህ ህመም ከተያዘ ግለሰብ ጋር የሚገናኙ ሁሉ በበሽታው ይያዛሉ ብለን እናስብ። እያንዳንዱ ታማሚ ከሁለት ሰዎች ጋር ይገናኛል ብንል፣ ትንሽ ሂሳብ ሠርተን በየቀኑ የሚኖረውን የህመምተኛ ብዛት ማወቅ እንችላለን።

የመጀመሪያው ህመምተኛ የተያዘበትን ቀን 1 ብለን ብንጀምር፣ የህመምተኞቹን ብዛት ለማወቅ የፈለግንለት ከዚህ ቀን ጀምረን በመቁጠር፣ ከሱ ቁጥር ላይ አንድ እንቀንንሳለን። ቀጥለንም ሁለት ቁጥርን (እያንዳንዱ ህመምተኛ ለሁለት ሰዎችን ሰለሚያስተላልፍ) በዚህ ቁጥር መጠን በራሱ ስናባዛው፣ በዚያች ዕለት የሚኖሩትን የህመምተኞች ብዛት እናገኛለ። የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ለምሳሌ በአሥረኛው ቀን ላይ የሚኖረውን የህመምኛ ብዛት ለማወቅ፣ ከአሥር ላይ አንድ ስንቀንስ ዘጠኝ ይሆናል፣ ሁለትን ዘጠኝ ጊዜ በራሱ ስናባዛ፣ ማለትም ሁለት ሲባአዛ በሁለት ሲባአዛ በሁለት ሲባአዛ በሁለት ሲባአዛ በሁለት… ዘጠኝ ጊዜ፣ 512 ሰው ይሆናል ማለት ነው።

10 – 1 = 9

2 X 2 X 2 X 2 X 2 X 2 X 2 X 2 X 2 = 512

ይህን ሂሳብ አንድ ህመምተኛ ሶስት ሰው ያገኛል ብለን ብንሠራው 10ኛው ቀን ላይ አስደንጋጩ አስራዘጠን ሺህ ስድስት መቶ ሰማኒያ ሶስት (19683) ብዛት ያህል ህሙማን የኖሩናል። ወይም በሂሳብ ቋንቋ አጻጻፍ የብዜቱን ለክ ከፍ በማድረግ፤

39 = 19683


አራት ሰው ቢያገኝ 10ኛው ቀን ላይ፤

49 = 262144 ህመምተኞች ይኖራሉ

በዚህ አይነት ቀለል ያለ ሂሳብ አሠራር ስለ የወረርሺኝ ስርጭት ግምት ማግኘት የሚቻል ሲሆን ካዕውነታው ጋር ለማዛመድ ግን ሌሎች ግብዓቶችን ማካተት ይኖርብናል። ከላይ የተመለከትነው አንድ ህመምተኛ ከሚገናኛችው ለሁሉም ህመሙን እንደሚያስተላልፍና ህመሙም የአንድ ቀን ቆይታ ብቻ ይኖረዋል ብለን ተነሳን። በተግባር ስናይ ግን የተላላፊ በሽታዎች ከህመምተኛው ተነስተው ወደሌላው የመተላለፍ አቅማቸው የሚለያይ ሲሆን፣ በተለያዩ ምክኒቶች ሳቢያ ግንኙነት ካላችው አንድም ግለሰብ ሳያስቀር የሚተላለፍ ተላላፊ ህመም አይኖርም። ተላላፊ ህመሞች አንድ ህመምተኛ ላይ የሚቆዩትና ሊስተላለፉ የሚችሉበትም ወቅት ከላይ እንደተመለከትነው አንድ ቀን ብቻም አይሆንም። እንዚህን ግብዓቶች ስናካትት በየቀኑ ይሚኖሩትን ህመምተኞች ብዛት ለማወቅ መሥራት ያለብን ሂሳብ የበለጠ ውስብስብ ይሆናል። በአጭሩ ግን አንጋፋው አይዛክ ኒውተን በቀረጸው ካልኩለስ በተባለ የሂሳብ ስልት በመጠቀምና በኮምቲዩተር በመታገዝ፣ ከተጋላጭ ህዝቡ በየቀኑ በህመሙ የሚያዘውን ክፍል ምን ያህል እንደሚሆን መገመት ያስችለናል።

ቀጥለንም ኮሮናን ወይም Covid 19ኝን ስንመለከት እስካሁን በተለያዩ ሃገራት ባለን መረጃ አንድ ታማሚ በአመካይ ከ 2 እስከ 6.6 ለሚደርሱ ሰዎች እንደሚያስተላልፍና የህመሙም ቆይታ ጊዜ 14 ቀን ያህል ሲሆን፣ ከ እንዚህ ቁጥሮች ተነስተን ህመሙ በህብረተሰቡ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ሊኖሩ የሚችሉትን ህመምተኞች ብዛት ስንመለከት እንደሚከተለው ይሆናል።

በአነስተኛው ብንሄድና አነድ ግለሰብ በህመሙ ወቅት ለሁለት ሌሎች ሰዎች ቢያስተላልፍ፣ ከፍተኛውን የህመምተኛ ብዛት - ከተጋላጭ ህብረተሰቡ 16 ከመቶ የሚሆነውን በ160ኛው ቀን አካባቢ ሆኖ እናገኘዋለን። ለማሳሌ ያህል የአዲስ አባባ ህዝብ ሁሉ ተጋላጭ እንደሆን ብናስብና ብዛቱም 5 ሚለየን በሆን፣ 16 ከመቶ ያህሉ 800 ሺህ ይሆናል ማለት ንው። በከፍተኝው 6.6 ከሄድን ደግሞ በ35ኛው ቀን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ህመምተኞች የምናይ ሲሆን ከህብረተሰቡ 57 ከምቶ ወይም ከ5 ሚሊየኑ 2.85 ሚሊየን ታማሚዎች የኖራሉ (ትንሽ በዛ)

ሂሳቡ የሚሰጠንን ትንበያ ከመረጃው ጋር ስናነጻጽር፣ የመጀመሪያው ህመምተኛመጋቢት 2012 መገኘቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ከተመረመሩት መሃል ከፍተኛ ከፍሉ ማለትም ከ10 እስከ 20 በመቶ ህመሙ የተገኘባቸው ወደ 140 ኛው ቀን አቅራቢያ ነኅሴ ውስጥ ሆኖ እንመለከተዋለን። ይህም ከመጀመሪያ ትንበያችን ብዙ አይራራቅም። በአንድ ቀንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን የተገኙት በዚሁ ወር ላይ ነው (1829 ህመምተኞች)። በጠቅላላው በዚህ ወቅት በምርመራ የተገኙት ህሙማን ቁጥር 15ሺህ ሲሆን፤ በትንበያው መሠረት ግን ነኅሴ ላይ ወደ 800 ሺህ ህሙማን መኖር እንደነበረባቸው ያመለክታል። ይህም የሚጠቁመን ከህሙማን መካካል እጅግ በጣም ጥቂቱን ነው በምርመራ እያገኘን ያለነው። እንዚህንም ብቻ በለይቶ ማቆያ ከተቀረው ህብረተሰብ መለይት ስርጭቱን ለመግታት ያለው ጠቃሚነቱን አጠያያቂ ያረገዋል።

ሌላው ከሂሳቡ የምናገኘው ትንበያ አሁን በታህሳስ ውር 2013የህመምተኞት ብዛት ከህዝቡ 0.3 ከመቶ መሆን እንዳለባቸው ሲሆን፣ ነገር ግን ሰሞኑን ያሉ መረጃዎች ከሚመረመሩት መካከል ከ5 እስከ 10 ከመቶ ያሉት ህመምተኞች እንደሆኑ ያመለክታል። መለስ ብለን ስንመለከት ምናልባት ከነኅሴ 2012 ጀምሮ ባለው ጊዜ ከተመረመሩት ከ5 እስከ 10 ከመቶ ህመሙ እንደተገኘባቸው የምናይ ሲሆን ይህ ቁጥር በጣም ከፍ ወይም ዝቅ የማለት ዝንባሌ አላሳየም። ይህም የሚነግርን በአማካይ አንድ ህመምተኛ በህመሙ ዋቅት ለአንድ ግለሰብ ብቻ እያስተላለፈ እያለ መሆኑን ነው። ቀድም ብለን ካየነው በአማካይ አንድ ህመምተኛ ለሁለት ግለሰብ ከማስተላለፍ ወደ አንድ ግለሰብ ብቻ ማስተላለፍ መቀነሱና በትንበያው መሠረት ወረርሽኙ ወደመጠናቅ አለመጠጋቱ (የሂሳቡ ወደተነበየው 0.3ከመቶ አለመውረዱ) ማናልባት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተወሰዱት እርምጃዎች ማለትም ርቅትን የመጠበቅና ማስክን የመልበስ፣ ተጋላጩ ወገን ሁሉ በህመሙ ሳይያዝ፣ የስርጭቱ ፍጥነት መቀነሱንና ከላይ እንደጠቀስነው አንድ ህመምተኛ ለአንድ ሌላ ግለሰብ ብቻ እያስተላለፉ ራሱን በመተካት ለይ እንዳለ መሆኑን መገመት የቻላል። ይህም ከሆነ ግን ትንሽ ጥንቃቄያችንን ከዘነጋን ወረርሽኙ መለሶ ሊያገረሽ እንደሚችል ማሰብ ይኖርብናል።

በቀጣይ ልጥፍ ከሌሎች በዓድገት የበለጸጉ ሃገራት ሲነጻጸር የኮሮና ህመም በሃገራችን የፈጠረው አስከፊነት አነስተኛ ይሆነበትን ምክኒያት አሁንም ከሂሳብ ጋር በማያያዝ ለመግለጽ እሞክራለሁ።

ይልጥፉ መረጃዎች የተገኙበት፤ Our World in Data፣ worldometer

ሂሳቡን የበለጠ ለመረዳት፤ Spread of Disease

ሂሳቡን ለመሥራት ሶፍውዌር፤ RKWard