ገፆች

ማክሰኞ 25 ፌብሩዋሪ 2025

ረቂቁ አቶም 4ሐ– ኤንዛይም ምንድነው

 

ኤንዛይሞች በሁሉም ፍጡሮች ውስጥ የሚገኙ እጅግ አስገራሚ ፕሮቲን ውህዶች ናቸው። ኤንዛይሞች አንድን ውህድ ከፋፍለው ወደ ሌሎች መጠናቸው ያነሱ ውህዶች፣ ወይም አነስተኛ ውህዶችን ገጣጥመው ተለቅ ወዳለ ውህድ የመቀየር ችሎታ አላቸው። ለምሳሌ ግልይኮጅን ሲንቴዝ (glycogen synthase) ሰውነታችን ለሃይል የሚጠቀምበትን ግሉኮዝ (glucose) የተባለውን ውህድ ሰውነታችን ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ሲሆን፣ ሃይልን ለማጠራቀም ወደሚያስችልው ግላይኮጅን (glycogen) ወደተባልው፣ ብዛት ያላቸውን የግሉኮዝ ውህዶችን ቀጣጥሎ በተለያዩ ይሰውነት ክፍሎቻችን ለሌላ ጊዜ ለማከማቸት ወደሚያስችለን መልክ ይቀይራል። በተቃራኒው ግላይኮጅኔዝ (glycogenase) የግሉኮዝ እጥረት ባለ ጊዜ ግላይኮጅንን መልሶ ወደ ግሉኮዝ በመቀየር ለሃይል ማመንጫነት እንዲያገለግል ያበቃዋል። ኤንዛይሞች ተግባሮቻቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜ በራሳቸው ላይ ምንም ለውጥ የማያስከትል በመሆኑ አንዱ የኤንዛም ውህድ መልሶና መላልሶ ሥራውን በተደጋጋሚ መፈጸም ይችላል። ይህን የመሰሉ ተግባራትን የሚፈጽሙ ወደ 75000 የተለያዩ ኤንዛሞች በሰውነታችን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በፊት በነበረው ልጥፍ የተመለከትነው አንጂዮ ቴንሲን ኮንቨርቲንግ ኤንዛይምም (Angitensin Converting Enzyme) ከንዚህ አንዱ ነው። ኤንዛይሞች በአባዛኛዎቹ የሰውነታችን ተግባራት ሚና ስለሚኖራቸው ከላይ እንዳየነው የተለያዩ ዘመናዊ መድሃኒቶችም እነሱን ኢላማ ያሚያደርጉ ናቸው። እነዚህ ድንቅ ፕሮቲን ውህዶች ከሚፈጽሟቸው ተግባርፕች መሃል የምንመገባቸውን ምግቦች መፍጨት፣ ሰውነታችንን መገንባት፣ ወደሰውነታችን የገቡ አደገኛ ንጥረ ነገሮችን (መርዞችን) ማምከን የመሳሰሉት ይገኛሉ። ቀደም ሲል ከተመለከትነው የደም ብዛት በተጨማሪ አንድ ሁለት ምሳሌዎችን ብንመለከት፣ አንዳንድ ወተት የማይስማማቸው ሰዎች ወተት ውስጥ የሚገኘውን ላክቶዝ (lactose) የተባለ ይስኳር አይነትን ወደ ሃይል ሰጭው ግሉኮዝ የሚቀይረው ላክቴዝ (lactase) የተባለ ኤንዛይም እጥረት ሲኖራቸው፣ የጨጓራ ህመም ያላቸው ደግሞ ፕሮቶን ፓምፕ (proton pump) የተባለው ኤንዛይም ከልክ ያለፈ አሲድ እንዲመረት የሚያደርግ ሲሆን፣ የህንንም ተግባሩም የሚከለክሉ ፕሮቶን ፓምፕ ኢንሂቢተር (proton pump inhibitor) የተባሉ መድኅኒቶችን (ለምሳሌ ኦሜፕራዞል – omeprazole) በመጠቀም ህመሙን ለመከላከል እንችላለን።