ገፆች

ሰኞ 2 ዲሴምበር 2024

ረቂቁ አቶም (ክፍል 4ሃ) - የደም ብዛት ህመም ምንድነው

በዚህ ልጥፍ የደም ግፊት ላይ ተዕጽኖ ያላቸውን ተቀያያሪ ነግሮችን መመልከት እንሞክራለን። በሚቀጥለው ልጥፍ የደም ብዛት ሰውናታችን ከሚገኙ ውህዶች ጋር ያለውን ግንኙነት እናያለን። የደም ብዛት ህመም ስንል በሰውነታችን የሚዘዋወረው የደም መጠን መጨመር ሳይሆን፣ በደም መዘዋወሪይ ቱቦዎች ላይ የሚከሰተው የደሙ ግፊት መጭመርን ያመለክታል። የግፊቱ መጠን በሁለት ዋና ምክኒያቶች ይወሰናል – የመጀመሪያው ልባችን የሚገፋው የደሙ መጠንና ሁለተኛው ደግሞ የደም ስሮቻችን ስፋት ወይም ጥበት ናቸው። ልባችን የሚገፋው የደሙ መጠን በተራው ሁለት ምክኒያቶች ይወስኑታል። የመጀመሪው ለባችን አንድ ጊዜ ሲመታ የሚገፋው የደም መጠንና ሁለተኛው ደግሞ ልባችን የሚመታበት ፍጥነት ነው። ይህን የበለጠ ለመረዳት ከሁሃ ፖምፕ ጋር ማነጻጸር እንችላላን። የፖምፑ ሞተር አንድ ጊዜ ሲዞር ከአንድ የልብ ትርታ፣ የፖምፑ ሞተር በደቂቃ የሚዞረው ፍጥነት ከልባችን ትርታ ፍጥነት፣ የውሃ መተላለፊያ ቧንቧዎች መጠን ደግሞ ከደም ሥሮቻችን ስፋት ይንጻጸራሉ። ስለዚህ እነዚህን ምክኒያቶች የደም ግፊት ላይ ያላቸውን ተእጽኖን ስንመለከት፣ ልብ አንድ ጊዜ ሲመታ የሚገፋው የደም መጠንና የትርታው ፍጥነት ሲጨምሩ፣ እንዲሁም የደም ሥሮቻችን ሲጠቡ የደም ግፊት እንዲጨምር ያረጉታል። ለምሳሌ የአትክልት ውሃ ማጠጫ ጎማን ስንመለከት፣ ቧንቧውን የበለጠ ስንከፍት ወደ ጎማው የሚገባው ይውሃ መጠን ይጨምርና ከጫፉ ሲወጣም የበለጠ ርቀት ይወረወራል። በርቀት የሚገኙትን ለማጠጣት ስንፈልግ ጫፉን በከፊል በጣታችን እንዘጋውና፣ ይህም በጎማው ውስጥ ያለውን ግፊት ስለሚጨምር አሁንም በበለጠ ርቀት ለማፈናጠር ያስችለናል። በጣም ቧንቧውን ከከፈትን ወይም ጫፉን ከልክ በላይ ከደፈንን ጎማው ሊፈነዳም ይችላል። በተመሳሳይ ሁኔታ የደም ሥሮቻችን ጠበው የደሙን ዝውውር ከከለከሉ፣ ደም ሥሮቻችን ሊጎዱና ሊፈነዱ ይችላሉ። በዚህ ዓይነት በአንጎላችን የሚገኙ የደም ሥሮች ሲፈነዱ ስትሮክ ተብሎ የሚጠራውን ህመም ያስከትላል። ስለዚህ ይህን ሰለ ደም ግፊት ካልን፣ ሰውነታችን ውስጥ ካሉት ውህዶች ጋር በምን ዓይነት ይገናኛል? ይህንን በሚቀጥለው ልጥፍ ከአንድ ለደም ብዛት ህመም ከሚሰት መድሃኒት አንጻር እንመለከታለን።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ