ገፆች

ቅዳሜ 1 ዲሴምበር 2018

ከሳይንስ አድማስ (01-2011) - ለልጆች የውፍረት መጠን ወላጆች ያላቸው ሚና


በጤና ሳይንስ ዘርፍ የአንድን ህመም መነሻን ለመረዳት ስንል ብዙ ጊዜ ሚገጥም ጥያቄ ይህ ህመም ከዘር በሚተላለፍ ጉድለት ነው አመጣጡ፣ ወይስ ከወሊድ በኋላ ከሚገጥሙን ከአካባቢያችን ወየም ከአኗኗራችን ከመነጩ ምክኒያቶች ነው ሊከሰት የቻለው የሚለው ነው። ከዘር ጉድለት የሚከሰተውን ለመከላከል ማረግ የምንችልው ውስን ሲሆን፣ ከአካባቢያችን ችግር ለሚከሰቱት ግን የተለያዩ እርምጃዎች የመውሰድ ዕድል ሊኖረን ይችላል ።ለምሳሌ ያህል እንደ ውባ ያሉት ተላላፊ ህመሞች መንሰኤ ሙሉ በሙሉ ከአካባቢያችን የምንጋፈጣቸው ጅርሞች ሲሆኑ፣ በሃገራችን ብዙ የማይታዩት ሲስቲክ ፋይብሮሲስና (Cystic Fibrosis) ፌኒልኬቶንዩሪያ (Phenylketonuria) የተባሉት ደግሞ ሙሉ በሙሉ በዘር ከሚተላለፉ ጉድለቶች የሚመጡ ናቸው። በርካታ ህመሞች ግን ሙሉ በሙሉ ከዘር ወይም ከአካባቢ ብለን በእርግጠኝነት መለይት አንችልም። ይልቅ ከዘር የሚተላለፉ ጉድለቶች ለአንዱ ወይም ለሌላው ህመም የሚያጋልጡን ሲሆን፣ ህመሙ እንዲከሰት ግን ተጨማሪ ከአካባቢያችን ወይም ከአኗኗራችን ጋር የተያያዙ ምክኒያት ወይም ምክኒያቶች ጋር መግጠም ይኖርበታል። በዚህም ዓይንት የሚከሰቱ የጡት ካንሰርና በአዋቂውች የሚታየው የስኳር በሽታ የገኛሉ።

ከህመም ሌላ ግን ከዘርም ከአካባቢም ተዕጽኖዎች የተለያየ መጠን ሊኖራቸው የሚችሉት የሰውነታችን ውፍረትና ቁመት ልክ ናቸው። በተለይም ብዙዎቻችን የልጆች ውፍረት መጠን ወላጆች በልጆቹ ላይ የሚተገብሩት የአመጋገብ ስርዓትን (ማለትም ከዘር ይልቅ ከአካባቢ ወይም ከአኗኗርያንጸባርቃል ብለን እናምናለን። ግን ምን ያህል እርግጠኛ መሆን እንችላላን?የህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ በጣም ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው አንደኛው ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴ የመንትዮሽ ጥናት (Twin Studies) የተባልውን በመጠቀም ነው። መንታዎች ሁለት ዓይነት ናቸው፣ ተመሳሳይ የሆኑና (Identical) ተመሳሳይ ያልሆኑ (Non-identical)። ተመሳሳይ የሆኑ መንታዎች የሚፈጠሩት ከአንድ የወንዴና ከአንድ የሰቴ የዘር ፍሬ ውህደት የተጸነሰው ህዋስ አንድ ልጅ መፍጠር ሲጠበቅበት ተከፋፍሎና ተለያይቶ ሁለት (አንዳንድ ጊዜ ከሁለትም በላይለጆች ሲያስከትል ነው ከወላጆቻቸው የሚወርሱት ዘርም አንድ ዓይንት ነው። ተመሳሳይ ያልሆኑት ግን ከሁለት የወንዴና ከሁለት የሰቴ የዘር የተጸነሱ ሲሆን፣ በተለያየ ጊዜ ከተወለዱ ለጆች ብዙ አይለዩም ዘራቸውም አንዳንድ ጊዜ ጾታቸውም የተለያየ ነው። ስንቀጥልም ያአንድን ህመም ወይም ባህርይ በህብረተሰቡ ያለውን ስረጭት ብንመለከት፤ ከተመሳሳይ መንታዎች በአንዱ ውይም በሁለቱ ላይ የሚታይብት ጊዜ ከማይመሳሰሉ መንትዮች ወይም መንታ ካልሆኑ ልጆች ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ፤ መንስኤው ከዘር እንዳልሆነ መደምደም እንችላለን። በአንጻሩ በሁለቱም ተመሳሳይ መንትዮች የሚታየበት ጊዜ ከሌሎቹ አብላጫ ካሰየ ግን ከዘር የመተላለፍ ዝንባሌ እንደሚኖረው እንደመድማለን።
ወደ ልጥፉ ርዕስ ስንመጣ በኪግክስ ኮሌጅ ለንደንና (Kings College London) በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን (University College London) በመተባበር፣ በሳስኪያ ሴልዛም (Saskia Selzam) መሪነት የተሰራው ጥናት፣ የለጆች ክብደት መጠን ከወላጆች ከሚያገኙት አመጋገብ ጋር ያለውን ግንኙንት ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል። ይልቅ ወላጆች የሚከተሉት አመጋገብ ስልት በተገላቢጦሹ የለጆቹን የውፍረት መጠን የሚከተል ሲሆን ይህ መጠን ደግሞ በአብላጫው በዘር የሚወሰን እንደሆነ ደምድመዋል። "ጥናታችን የሚያሳየን ወላጆች የሚከተሉት የአመጋገብ ስርዓት የልጆቹን ወፍራም ወይም ቀጭን የመሆን ከዘር የመጣ የተፈጥሮ ዝንባሌን የተከተለ ነውብለዋል።እዚህም ድምዳሜ ላይ የደረሱት ክ1994 እስከ 1996 በእንግሊዝ ሃገር የተወለዱ 4500 ጥንድ መንትዮችን በማጥናት ነው። ሳይንቲስቶቹ ጥናቱን የሠሩት የልጆች የክብደት መጠን በየጊዜው እየጨመረ ለመሄዱ ዝንባሌ ምክኒያት ሊሆኑ የሚችሉ የአካባቢ ተዕጽኖዎችን ለመለየት ሲሉ ነው። እስካሁን ባለን ልምድ የሚበሉትን መጠን እንዲቀንሱ ጫና ሚደረግባቸው ልጆች የመወፈር ዝንባሌ እንደሚኖራቸው (ቁጥጥር በሌለበት ሰዓት የተከለከለ ነገር ሁሌ ስለሚያምረን ያጡት የመሰላቸውን ላማካካስ ስለሚጥሩ፣ እንዲጨምሩ የሚጫኗቸው ደግሞ ከመናሻው አነስተኛ የምግብ ፍላጎት ያላቸው ልጆቹ ላይ ጭንቀት ስለሚያስከትል እንዲያውም የበለጠ የምግብ ፍላጎታቸውን እንደሚያዳክም ይገመታል። ነገር ግን ደግሞ የሰውነታችን ውፍረት መጠን በዘር የመተላለፍ ዝንባሌ እንዳለው ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህም ጥናት በተጨማሪ የሚይመለክተው ወላጆች ይህንን ከዘር እሚገኘውን ዝንባሌ በመከተል ነው የአመጋገብ ሥራዓታቸውን የሚያስተካክሉት እንጂ እንደምናስበው ከየራሳቸው ተነሳሽነት ውይም ጸባይ የሚወሰን አይደለም። ጥናቱም መንትዮቹ በዘር የሚወርሱትን የመወፈር ዝንባሌን (ዲ ኤን ኤ – DNA) መርምረው ይሕም ከላይ የተገለጸውን ወልጆች በልጆቻቸው ላይ ከሚተገብሩት የአመጋገብ ሥራዓት ጋር እንደሚዛመድ አረጋግጠዋል።
ይህ ጥናት የሚያስገነዝበን ልጆች በሚመገቡት መጠንና ቀጥሎም ለውፍረታቸው ወላጆች ያላቸው ሚና ወይም ተጠያቂነት ውስን እንደሆነ ነው (የምግብ እጦት ደረጃ መለስ)። ልጆቹ የሚመገቡትን መጠን በጥብቅ መቆጣጠር ጥቅም ወይስ ጉዳት ይኑረው ጥናቱ ሊነግረን አይችልም። ለረጅም ጊዜ ብዙ ልጆችን ከጨቅላ ዕድሜ እስክ ልጅናታቸው ማገባደጃ ድርስ የሚከታተል ጥናትም (Longitudinal Study) ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት ያስችለናል ሲሉ አጥኚዎቹም ጽሁፋቸውን አጠቃለዋል።

ማክሰኞ 19 ጁን 2018

ረቂቁ አቶም (ክፍል 1ለ) - አቶምን እንዴት አየን?


በክፍል 1ሃ ለአቶም መኖር መረጃ ያልኩትን ብራውኒያን እንቅስቃሴ (Brownian Motion) መጀመሪያ ከተመለከትኩበት የልጅነት ዕድሜዬ ብዙ ዓመታት ያለፉ ሲሆን፣ አሁን ለትውስታ በድጋሜ ለማየት ሞክሬ ውጤቱንም ከታች ባለው ምስል ለማስተላለፍ ሞክሬያለሁ። ቅንታት የዱቄት ወተት በውሃ በመበጥበጥና ትንሽ ያህሉን ምስሉ ላይ እንደሚታየው የማጉያ መነጽር ስላይድ (Microscope Slide) በሚባል መስታውት ላይ በማድርግ፣ ዲጂታል ካሜራ በተገጠመለት ማጉያ መነጽር አማካይነት በኮምቲዩተራችን ልናይበት በምንችለው በፊልም መልክ ከዚህ ልጥፍ ጋር አያይዣለሁ። በትኩረት ሰንመለከት ጠቆር ያሉ የመንቀጥቀጥ ዓይነት እንቅስቃሴ የሚያሳዩ አካሎች የሚታዩ ሲሆን፣ እነዚህም በጣም ጥቃቅን የወተቱ ብናኞች ሲሆኑ ሊታዩ በማይችሉት በውሃው አቶሞች በመገጫጨታችው ነው በዚህ መልክ ሊጨፍሩ የቻሉት። መልካም ዕይታ!



  

ሐሙስ 3 ሜይ 2018

ረቂቁ አቶም (ክፍል 1ሃ) - የሁሉም ነገር መነሻ

በአስር ዓመቴና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያልሁ ነው አንዲት መጽህፍ ልመለከት የቻልኩት። ይህች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተጻፈች "ዘ ቴሌስኮፕ ኤንድ ማይክሮስኮፕ" (The Telescope and Microscope) አርስት የነበራትና ለልጆች እንዚህን መሳሪያዎች ለማስተዋወቅ ተብላ የተጻፈች ነበረች። በቀጣዩም ህይወቴ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ላለኝ ከፍተኛ ዝንባሌና አክብሮት መነሻ እቺ ትንሽ መጽሃፍ ነበረች ለማለት ያስደፍረኛል ። በከፍተኛ ደረጃ የምንመካበት ለማየት ችሎታችን ምክኒያት የሆንው ዓይን የተባለው የሰውነት ክፍላችንን ድክመት በማጋለጥ፣ ለነዚህ መሳሪያዎች ባይሆን ልናየው የማንችለው ሌላ ድብቅ ዓልም መኖሩን ተገነዘብኩ። እንደዕድሌም ሆኖ በልጅነቴ ከአባቴ ጓደኛ በስጦታ አንድ የልጆች ማይክሮስኮፕ፣ ከዚያም ሁለትኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ቤተሰቦቼን በመጭቅጭቅ ጥራት ያለው ለምርምር የሚበቃ ማይክሮስኮፕ ባለቤት ለመሆን ችዬ ነበር። እንዲሁም ከዚች መጽህፍ ካገኘሁት መረጃ ከዓይን መነጽር በተገኘ መስታወት ደከም ያለ ቴሌስኮፕ መስራት ችዬ ነበር። በተለይ በማይክሮስኮፖቹ በግቢያችንና በአካባብያችን በሚገኙ ውሃ አካሎችን በመመርመር ብዙ ሰዓታትን አሳልፍ ነበር። እግረመንገዴንም ለአቶሞች መኖር ዋነኛ ማስረጃዎች ለአንዱ ምስክር ልሆን ችያለሁ።
ወደ አርስታችን ስንመለስ አብዛኛዎቻችን ሁሉም ነገር እጅግ በጣም ረቂቅ ከመሆናቸው የተነሳ በምንም ዓይነት ማጉያ መሣሪያም ቢሆን በነጠላ ለመመልክት ምንም ተስፋ በሌለን አቶም በተባሉ አካሎች እንደተሠራ እናውቃለን ወይም እንሰማለን። ሁሉም ነገር በምድርም በሰማይም ከአቶም ነው የተሠራው ካልን በመጠኑ እነዚህን ስውር ነገሮች መረዳት ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ግለሰብ (በአቶም የተሠራ እንደመሆኑ መጠን) የስኳር ህመም አለበት ከተባለ፣ አቶሞቹ በዚህ ጉዳይ ምንድነው ሚናቸው? የአዕምሮ ህመምስ ቢሆን። የምንበላው የምንጠጣው፣ የምንጓጓዝበት፣ በርቀት የምንነጋገርብት፣ የምንለብሰው፣ የምንጠለልበት ሁሉም ከአቶም ነው የተሠራው ካልን፣ ይህን ሁሉ የመገንባትና የማቀፍ ችሎታ ያለው አቶም ምንደንው? አቶሞችን በምንም ዓይንት መመልከት የማይቻል ከሆን ለመኖራችው ምን መረጃ አለን? እነዚህን ምሰል ጥያቀዎችን ለመመለስ ወደኋላ ብለን የግኝታቸውን ታሪክ መመልከት ይኖርብናል።
የተለያዩ ጥንታዊ ህብረተሰቦች በጣም በርካታና ውስብስብ የሆኑ የሚመለከቷችውንና ይሚገለገሉባቸውን የተለያዩ ነገሮችን ሁሉ የተሰሩባቸው ነጥረ ነገሮች ብዛት ምናልባት ከማሰብ ከመረዳትና ከመቁጠር አቅማችው በላይ ሲሆኑባቸው ሳይሆን አይቀርም፣ ጉዳዩን ለማቃለል እነዚህ ሁሉ የተሠሩት ጥቂት ውስን የሆኑ ንጥረነገሮችን በተለያየ መጠን በመቀላቀል ሊሆን ይቻላል ብለው የገመቱት።
ለምሳሌ ጥንታዊ ግሪኮች ሁሉም ነገር ከአራት ብቻ ንጥረ ነገሮች የተሠሩና እነዚህም ምድር፣ አየር፣ እሳትና ውሃ ሲሆኑ፣ ከበድ ያሉት የምድሩ መጠን የበዛ ሲሆን፤ ቀለል ያሉት ደግሞ በብልጫ አየር ይይዛሉ ወዘተ… ሲሉ ለዚህም ዕምነት ምንም አይንት ግልጽ መረጃ ሳይኖራቸው በበለጠ ከፍልስፍና ከጥንቆላ ጋር ያያይዙት ነበር።
የመጀመሪያው አቶም ለመኖሩ ግልጽና አሳማኝ መረጃ የተገኘው እንደ አውርፓውያን አቆጣጠር አስራዘጠነኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያው ላይ ጆን ዳልተን በተባለ ግለሰብ አማካይነት ሲሆን፣ እሱም አንዳንድ ንጥረ ነገሮች ሲቀላቀሉ የሚፈጠረው አዲስ ነጥረ ነገር ውስጥ የሚኖራቸው ተመጣጣኝንት፣ ሁልጊዘም በአነስተኛ ቁጥር ክፍልፋይ እንደሆነ ታዘበ።
በተጨማሪም የቅልቅል ውጤቱን መልሰን ወደ መነሻ ንትረ ነገሮቹን ብንለያይ፣ የፈለግንውን ያሁል መጠን ብንሰፈር የመነሻዎቹ ክፍልፋይ አይለያይም። በጣም ትንሽ መጠን ሰፍረን አንድ እጅ ለሁለት እጅ ካገኘን፣ መካከለኛ ስንሰፍር ያንኑ አንድ እጅ ለሁለት እጅ ነው የምናገኘው። ብዙም ብንሰፍር እንደዚያው ። ለምሳሌ ክፍልፋዮቹ አንድ ለአንድ፣ አንድ ለሁለት፤ ሁለት ለሶስት፤ አንድ ለአራት ሊሆኑ ሲችሉ አ ንድ ለዘጠን፤ አምስት ለአስራሰባት፤ አስራሶስት ለመቶ ዓይነት ክፍልፋዮች ግን ሲሆኑ አይታይም። ይህን የመሰለ ውጤት ማግኘት የምንችለው ማንኛውም ነገር በማይከፋፈሉ በሙሉ ቁጥር ብቻ በሚዋህዱ ረቂቅ አካሎችን በማብዛት የተገነቡ ሲሆን ብቻ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም። ሌላው ለአቶም መኖር የተግኘው መረጃ እንደ አውርፓውያን አቆጣጠር 1827 ዓም በእጽዋት ተመራማሪው ሮበርት ብራውን ሲሆን በማጉያ መነጽር ውሃ ውስጥ ያሉ የአዋራ ብናኞችን ሲመለከት ያለማቕርጥ በተለያየ አቅጣጫ ሲወርጩ ታዘበ። እኔም በለጅነቴ ለመመልከት ዕድል የነበረኝ ይህንኑ ነበር። ለዚህም ክስተት ምክኒያት ብናኞቹ በውሃው አቶሞች በመገጫጨታቸው መሆኑን ገመተ። ቆየትም ሲል በ1905 አልበርት አይንሳታይን የዚህን እንቅስቃሴ ባህርይ ሳይንሳዊ በሆነ አካሄድ አብጠርጥሮ ከተነተነ በኋላ፣ ጂን ቴሪን የተባለ ሳይንቲስት እንቅስቃሴውን በጥንቃቄ በመለካት የአቶሞችን ክብደተና ስፋት መገመት ችሏል።
በክፍል ሁለቱ ልጥፍም ስለአቶሞቹ መጠንና ዓይነት፣ እንዲሁም ስለውህደታቸውና ከሒወታችን ጋር ስላላቸው ቁርኝት አንዳንድ ነጥቦችን ለመግለጽ እሞክራለሁ።


ዓርብ 20 ኤፕሪል 2018

ምን ያህል ውሃ (እንዲሁም ምግብና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን) መውሰድ አለብን? - የመረጃዎቹ ሳይንሳዊ መሠረት

ሲ ኤን ኤን (CNN) በቅርብ ጊዜ በድረ ገጹ ላይ (http://edition.cnn.com/2017/09/27/health/benefits-of-water-and-fluids/index.html) እንዲሁም ሌሎች የውጭ እና የሃገር ውስጥ የሚዲያ አውታሮች በቀን ውስጥ ምን ያህል ውሃ መጠጣት እንደሚኖርብን ሲነግሩን፣ ወንዶች 3.7 ሌትር በቀን ሴቶች ደግሞ 2.7 ሌትር በቀን እንደሆነ ይመክሩናል። ለዚህም መረጃ መነሻው የአሜሪካው የሳይንስ የምህንድስናና የህክምና ምርምር ተቋም (The National Academies of Science Engineering and Medicine) የውሃና የተለያዩ ለሰውነታችን የሚያስፈልጉ ንጥረ ነገሮችን የምንወስድበት መጠን ከሚገልጸው ህትመት (Dietary Reference Intakes: Water, Potassium, Sodium, Chloride and Sulphate - https://www.nap.edu/read/10925/chapter/1) ሲሆን፣ ጠለቅ ብለን ጉዳዩን ስንመለከት ግን መውሰድ ያልብንን የውሃ መጠን መወሰን በሚዲያዎቹ እንደተገለሰው ያህል ግልጽ አለመሆኑን እንረዳለን።
የውሃውን መጠን ጉዳይ ከመመልከታችን በፊት ግን በጥቅሉ ለጤናችን የሚያስፈልጉን የተለያዩ የምግብና የመጠጥ መጠኖችን እንዴት ነው ማወቅ ወይም መገመት የምንችለው? ይህን ለመመለስ በሳይንሳዊ ሂደት ምን ዓይነት ጥናቶችን መተግበር እንደምንችልና ከጥናቶቹ የሚገኙ መረጃዎች አስትማማኝነትን በዚሁ ህትመት በመጠኑ ተብራርተዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ የተጠቀሰው በላብራቶሪ እንሰሳት ላይ የሚደረግ ጥናት ሲሆን፣ የዚይ ዓይነት ጥናት ጥንካሬው በረቀቀ ሁኔታ ለእንሰሳቱ የሚሰጡትን የምግብና የንጥረ ነገሮችን መጠኖች መቆጣጠር ሲቻል፣ እንዲሁም ከእንሰሳቶቹ ዘር ጾታ ወይም አካባቢያዊ ለዩነቶች በጥናቱ ልይ ሊኖራቸው የሚችለውን ተዕጽኖ በአግባቡ መለየት ያስችላል። በሌላ ጎኑ ግን እንሰሳትና ሰው የስውነት ትግባራቶቻቸው ላይ ልዩነቶች በመኖራቸውና፣ ላብራቶሪ ውስጥ ልናገኛቸው የምንችለው ጥብቅ የሙከራ ሁኔታዎች በነጻነት ወይም በተፈጥሮአዊ ሁኔታ ለሚኖሩት ሙሉ ለሙሉ አመላካች ሊይሆኑ አለመቻላቸው የገኛሉ።
በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠውን ስንመለከት፣ በጥናት ማዕከል ውሰጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሚመገቡትን በመመጠንና በመቀያየር የሚሠራ ጥናት ነው። የተለያዩ አመጋገብ ዙሪያ የምናገኛቸው መረጃውች አብላጫዎቹ በዚህ ዓይነት የተገኙ ሲሁን የህም የጥናት ዓይነት የራሱ ድክመቶች ይኖሩታል። እነዚህም በሰው ላይ የሚሠሩ ጥናቶች ለውስን ጊዜ ስለሚካሄዱ በረጅም ጊዜ የአመጋገብ ባህረዮች ያለቸውን ጥቅምና ጉዳት መገመት አለማስቻል፣ ጥናቱ ላይ የሚሳተፉት አነስተኛ ቁጥር ከመሆኛቸው ውጤቱ ላይ የሚኖረን መተማን ደረጃ የመቀነስና እንዲሁም በጥናት ማዕከል ውስጥ የሚሠራው ምን ያህል ቀን እስተቀን ኑሮውን ወደሚያካሂደው በቀትታ አመላካች መሆን አለመቻሉ ይገኙበታል።
ሶስተኛው የጥናት ዓይነት የለት ተለት ኑሮዋቸውን እያካሄዱ ያሉ የሀብረተሰቡ አባላትን በመመልከትና የተለያዩትን አመጋገብ ባህርይዮች በህብረተሰቡ ከሚታዩ የጤና ጉድለቶች ጋር ለማዛመድ መሞከር ሲሆን፣ የዚህ ዓይነት ጥናት ችግር የታዩት የአመጋገብ ባህርዮች በቀጥታ የጤና ጉድለቶቹን ለማስከተላቸው ወይስ ከሌላ ግምት ካልተሰጣቸው ወይም ከተደበቁ ነባራዊ ሁኔታዎች የተከተሉ ለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አለመቻል ነው። ብዚህ አይነት የተገኘ መረጃን ለማጠናከር የተለያዩ ህብረተሰቦችን ደጋግሞ ማጥናትና የጥናቱ ተሳታፊዎች ማብዛት መፍትሄ ሊሆን ይችላል።
አሁን ግን ወደ ውሃው ጉዳይ ስንመለስ ጽሁፉ የሚነግረን በአሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ከ19 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ያሉ ውንድና ሴት የህብረተሰብ አባላት ለተላከ መጠየቂያ ምላሾች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ እነዚህ አባላት የሚጠጡት አማካይ የውሃ መጠን ለአብዛኛው ሰው በቂ ይሆናል ተብሎ ስለሚገመት ነው። ጽሁፉ በዙ የሚንቀሳቀሱ ወይም መቆታማ አካባቢ ያሉ ከተጠቀሰው መጠን የበለጠ መውሰድ ሊኖርባቸው እደሚችልም ይገልጻል።
ነግር ግን የአሜሪካውን በቀጥታ ለራሳችንም እንደሚሆን መቀበል አለብን ወይ? በአንደኛ ደረጃ ከአሜሪካው የሚለየን አማካይ የሰውነታችን ክብደት ሲሆን፣ የአመሪካው 80.7 ኪሎግራም ሲሆን የኛ ደግሞ 60.7 ኪሎግራም ነው። ከዚህ ብቻ ተነስተን የተጠቀሱትን ቁጥሮች 75 ከመቶ በመቀነስ ለወንዶች 2.8 ለሴቶች ደግሞ 2.0 ሌትር ይሆናል ማለት ነው። ሌላው መገንዘብ ያለብን የተጠቀሱት ቁጥሮች በመጠጣት ብቻ ሳይሆን ከምግብም የምናገኘውን ውሃ ያጠቃለሉ እንደሆኑና ብዙ የምንመገባችውም ከፍተኛ የውሃ ይዘት ይንዳላቸው ነው። ለምሳሌ ዳቦ 40 ከመቶ ስጋ ከ55 እስከ 77 ከመቶ እንቁላል እንደአሠራሩ 63 እስከ 75 ከመቶ አትክልትና ፍራፍሬ እስከ 97 ከመቶ ይገኙባቸዋል። ስለዚህም በቀን ውስት የተመገብነውን ግምት ውስጥ በማስገባት በውሃ መልክ የምንወስደውን መመጠን እንችላለን ።

ለማጠቃለል በዚህ ልትፍ ለማስተላለፍ የሞከርኩት አመጋገብን በተመለከተ ምንም የማያወላውል መቶ በመቶ እርግጠኛ የሆነ መርረጃ ማግኘት በጣም ከባድ መሆሁንና፣ በሚዲያ የሚተላለፉ ምክሮች በርካታው ደካማ፣ አጠያያቂ ወይም ስተታማ ሳይንሳዊ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ እንደሚችል በመገንዘብ፣ በጥርጣሬ ዓይን መመልከት እንደሚኖርብንና ከነዘኢህ መረጃ ተነስተን በኑሮዋችን ለይ በምናረግው ለውጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግው ነው።  

ዓርብ 19 ጃንዋሪ 2018

ሰይንስና ዘመናዊ ህክምና - እንዲሁም ስለ ታይፈስና ታይፎይድ

ይህን ልትፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ የዘመናዊ ህክምና ትምህርት ዲግሪ ባለቤት ከመሆኔ ዘንድ ስመለከት፣ በለፉት ዓመታት ለበርካታ ህሙማን የታይፈስና የታይፎይድ  በሽታዎች እንደተገኙባቸውና ከነዚህም በሽታዎች ለመፈወስ የሚያስፈልጉትን አንቲባዮቲክ የተባሉ መድሓኒቶች ሲታዘዝ በመታዘቤ ነው። ዘመናዊ ህክምና ከባህላዊ ህክምና የሚለይው በዋነኛነት ዘመናዊው ህክምና ሳይንስ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። ይህም ማለት የህመሙን ዓይነት ለይቶ ለማውቅ፤ ህመሙ ሰውነት ላይ ያስከተለውን በደል ለመረዳት፤ ለህመሙ የሚደረገውን የህክምና እርምጃ ለመወሰን፤ የህመምተኝው ወደፊት ዕጣ ፋንታ መገመትን የመሳሰሉት በሳይንሳዊ ምርምር  በተገኙ መረጃውች ላይ የተመሰረቱ ምሆን የኖርባቸዋል። ይህን ካልን ስለ ታይፈስና ታይፎይድ ሳይንስ ምን ይነግረናል?
በመጀመሪያ  ታይፈስን ብንመለከት -  ታይፈስ በአንዲት ውስን ዓይንት በለምድ ጀርም በለን ከምንጠራቸው አንዱ (ሳይንሳዊ ስያሜው ሪኬትሲያ ፕሮዋዜኪአይ  - Rickettsia prowazekii) የሚከሰትና በሰውነት ቅማል ዓማካይነት የሚተላለፍ የህመም ዓይነት ናው። ይህም ህመም ዋነኝው ምልክቱ ድንገተኛና ከፍተኛ ትኩሳት ሲሆን በተጨማሪ ከባድ ራስ ምታትና ሌሎችም ምልክቶች ይኖረዋል። ብዙውን ጊዜ የሚከሰተውም ቅማል ከሰው ወደሰው ሊዛመት በሚችልባቸው ንጽህና በጎደለባቸውና በተጣበቡ ሁኔታዎች - ለምሳሌ በወይኒ ቤቶች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች መጠለያ የመሳሰሉት ነው። ህመሙም ሲከሰት በአብዛኛውም ጊዜ አንድ ነጠላ ሰው ብቻ ላይ ሳይሆን የሚታየው በአጭር ቀናት ውስጥ በጥቂት ግለሰቦች ላይ ወይም በወረርሺኝ መልክ ይሆናል። እነዚህን ሁሉ ግምት ውስጥ ከተን ባአንድ ጥሩ ኑሮ ደረጃ ላይ ያለና ንጽህናው የተጠበ ግለሰብን ታይፈስ አለብህ ሲባል ጥርጣሬ አያስነሳም ወይ።
ታይፎይድን ስንመለከት ደግሞ አሁንም በአንድ ውስን ጀርም (ሳልሞኔላ ታይፊ - Salmonella typhi) አማካይነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ሲሆን፣ የሚተላለፈው ባዓይነ ምድር በተበከለ ውሃ ወይም የምግብ ዓይነቶች አማካይንት ነው። ምልክቶቹም አሁንም ከፍተኛ ትኩሳትና ራስ ምታት ሲገኙባቸው እንዲሁም የሆድ ህመም፣ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ ሊኖሩ ይችላሉ። የሚተላፈው በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ ስለሆን ግን የታይፈሱን ያህል የንሮ ደረጃ ላይለይ ይችላል።
እነዚህ ሁለት ህመሞች አንድ ግለሰብ ላይ ለመኖራችው ማረጋገጥ ግን የሚያስቸግርብት ምክኒያት ምልክቶቹ ከሁለቱም መካከልና እንዲሁም ከበርካት ሌሎች በሽታዎች - ለምሳሌ ሃይለኛ ጉንፋን ጋር መመሳሰላቸውና መደራረባችው ነው። በምልክቶቹ ብቻ ለመወሰን ስለሚያስቸግርም የነዚህ ህመሞች መሮር ሲጠረጠር በህክምና ባለሙያዎች በደም ላይ የሚሠሩ ምርመራዎች ይታዘዛሉ (ዊዳል እን ቫይል ፌሊክስ - Widal, Weil Felix)። እነዚህም ምርምራዎች ፖዘቲቭ (Positive) ካሳዩ ከሁለቱ አንዱ ወይም አንዳንድ ጊዜ ሁለቲም ህመሞች  ባንድ ጊዜ እንደተከሰቱ በመቁጠር ተገቢው መድሃኒት ይታዘዛል።
ነገር ግን ትልቁ ችግር ካላይ የተጠቀሱት የደም ምርምራዎች የሁለቱንም ህመም መኖርን ማርጋገጥ ችሎታችው በጣም ውስን ከምሆኑ የተናሳ ምናልባት ከንጭራሹ መታዘዝ የለባችውም ያስብላል። ይህንንም ለመረዳት ሙያው ልይ ላልሆን ሰው በጣም ቀላል ባይሆንም በቀጣይ ልጥፎች ከሌሎች የሳይንስ መረጃዎች ጋር በማዛመድ ለመተንተን እሞክራለሁ። ለጊዜው ግን በአጭሩ ምርመራዎቹ በቀጥታ ጀርሞቹ በሰውነት ውስጥ መኖራችውን ወይም አለመኖራቸውን ሳይሆን ይሚነግሩን የተለያዩ ህመሞችን ለመከላከል ብሎ አካላችን የሚያመንጨው አንቲቦዲ (Antibody) የተባሉ ንጥረ ነገሮችን ነው የሚለኩት። እንዚህ አንቲቦዲዎች ለአንዳንድ ህመሞ ዓይንት ጥሩ እመላካች ቢሆኑም  (ለምሳሌ ለኤች አይ  ቪ) ለታይፈስና ታይፎይድ ግን በከፈተኛ ደረጃ ህመሙ በሌለባቸው በርካታ ሰዎች የተሳሳተ ማረጋገጫ እንደሚሰጡ ጥናቶች አሳይተዋል። በተለይ ለታይፈስ የሚሠራው ቫይል ፌሊክስ ምርመራ ህመሙ ከሌለባችው መካከል ሃምሳ ከመቶውን የተሳሳተ መረጃ ሊያመለክት እንደሚችል ታይቷል።
ሳይንስና ዘመናዊ ህክምና በከፈተኛ ደረጃ የተጠላለፉ እንደመሆናቸው መጠን ባለሙያዎቹም በሥራቸው ሂደት ይህንን ባይዘነጉ፣ በዘርፉ ያሉት የመንግሰት ቁጥጥር አካሎችም በላብራቶሪ ምርመራ ጥራትና  ለሃገራችን ሁኔታ ተገቢነታቸው ላይ ተኩረት ቢሰጥ፤ በህብረተሰቡም  ዘንድ  ስይንስ ላይ ያለው ግንዛቤን  ለማሻሻል ጥረት ቢደረግ ፣ በታይፈስና ታይፎይድ ላይ የታየውንና ሌሎችንም ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት ላይ ሊሠሩ የሚችሉ ስህተቶች መስፋፋትን በበለጠ ለመከላከል ይቻላል።  

እሑድ 7 ጃንዋሪ 2018

ሳይንስ የሚነግረን አስደናቂ መረጃዎች

ሳይንስ እጅግ በጣም የሚደንቁና ለመረዳትና ለማመን የሚያዳግቱ የተለያዩ መረጃዎችን በየጊዘው ይፋ ያረጋል። ሁሉም ነገር አቶም በተባሉ በጣም ረቂቅ ከመሆናቸው የተንሳ በምንም ዓይነት ማጉያ መሳሪያ የማይታዩ አካሎች እንደተሰራ ይነግረናል። ምድር ጸሓይን በዓመት ዓንድ ጊዘ በመቶ አምሳ ሚሊዮን ኪሎመትር ርቀት እንደምትዞርና መካከልዋ ላይ ድፍን ብረት አንኳር እንዳላትም፣ በህዋው ውደ አስር ሺህ ቢልየን ቢሊይን ክዋክብት እንደሚገኙ የመሳሰሉትን ይዘግባል። የአንድን ሰው አካል ለመሥራት የሚያስፈልግው ሙሉ ፕላን እዚህ ንባብ ላይ ካሉት አራት ነጥብ አንዷን ከማያክል ቅንጣበ ህዋስ ከዘር ወደዝር እንደሚተላለፍ፣ የአንድ አካል ቅሪት ዕድሜ ሶስት ሚሊየን ዓመት እንደሆነ፣  እንጭት ከአየር ፣ ክውሃና ከጸህይ ብርሃን ተቀምሞ በአትክልቶች እንደሚሠራ... እነዚህን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ክስተቶችን እንዴት ብለን ነው ለማወቅ የቻልነው? ዓይናችንን ጭፍነን ትክክለኝታቸውንስ መቀበልስ አለብን ወይ? እነዚህ መረጃዎች ትምህርት ላይ ሳለን በመምህራኖቻችን የሚነገሩን ቢሆንም እንዴት ተብሎ እንደተደረሰባቸው በዝርዝር አይገለጽልንም። እነዚህንና ሌሎች ከሳይንስ የምናገኛቸው መረጃዎች በምን ዓይነት ምርምር ሂደት ሊገኙ  እንደተቻሉና መረጃውን ስላገኙ ሳይንቲስቶች፣ እንደሁም በግኝቱ ጊዜና የአካባቢ ስለነበሩው ማህበራዊ ሁኔታ አጠር ባለ መልክ በቀጣይ ልትፎች ለመዳሰስ እሞክራለሁ።