በቀድሞው ልጥፍ በዘር ለሚተላለፉ ባህርዮች መረጃ፣ በሰውነታችን ህዋሶች በሚገኘው በDNA አማካይነት እንደሆነ ተረዳን። ይህ መረጃ ግን እንዴት ነው ወደ ባህርዮቹ የሚተረጎመው? ጥያቄው ከተፈጥሮ ክስተቶች እጅግ አስደናቂ ከምንላችው አንዱ ወደሆነው የኑክሌዪክ አሲድና የፕሮቲን ተስስር ወየም ጥምረት ይወስደናል። የዚህን ሂደት ተዓምራዊነቱን በቃል መግልጽ ቢያዳግትም ቀለል ባለ መልኩ እንደሚከተልው ነው።
በቀድሞ ልጥፍ የDNAን ቅርጽና እንዴት የራሱን ግልባጭ መፍጠር እንደሚችል ተመለከትን። እንዲሁም በኑክሌይክ አሲድ ቅደም ተከተል ይዘቱ በዘር የሚተላለፉ ባህርዮች መረጃን እንደሚይዝም ተረዳን። በ1953 አካባቢ ይሩሲያው ሳይንቲስት ጆርጅ ጋሞቭ (George Gamow) በተፈጥሮ የሚገኙት 20 አሚኖ አሲዶቹ እያንዳንዱ በሶስት በሶስት ኑክሌዪክ አሲድ ጥንዶች እንደሚወከሉ ተነበየ። ይህ ማለት አራቱ ኑክሌዪክ አሲዶች በተለያይ ዓይነት እና ቅደም ተከተል ሶስት ሶስት ጥንድ ሲሆኑ በአጠቃላይ 64 አሚኖ አሲዶችን ሊወክሉ ይችላሉ።
ሶስት ሶስት የኑክሌዪክ አሲድ ጥንዶች የሚያመለክቷቸው አሚኖ አሲዶች [1]
ጋሞቭ ይህን ከተነበየ ብኋላ በ1961 አካባቢ በተለያዩ ሳይንቲስቶች ላቦራቶሪ ውስት በተሠሩት ሙከራዎች ሙሉ ጄኔቲክ ኮድ ተብሎ የተጠራው ሶስት ሶስት ኑክሌዪክ አሲዶችን ከእያንዳንዱ 20 አሚኖ አሲድ ጋር ከላይ ባለው ሰንጠረዥ መሥረት ማዛመድ ተቻለ። የሰውነት ህዋሶቻችን በዚህ ኮድ መሠረት ከDNAው ተነስተው ፕሮቲን የሚቀርጹበትም ሂደት እንደሚከተለው ሲሆን፣ ሌላም ኑክሊዮታይዶችን በመቀጣጠል የተሠራ RNA የተባል ትልቅ ውህድ ተሳትፎን ያካትታል።
መጀመሪያ ሥራ ላይ እንዲውል የተፈለገውን ዘረ መል ያካተተው ይDNA ክፍል እንደዚፕ በመሃሉ ላይ ይሰነጠቃል። ቀጥሎም DNAው ላይ ያሉትን ኑክሊዮታይዶችን ሚገጥሙ ነጠላ ኑክሊዮታይዶች እይመጡ ቦታ ቦታቸው ላይ ይገጣጠሙና እርስ በዕርስ ይያያዛሉ። ይህ ይሚካሄድው በህዋሱ ኑክሊይስ የተባልው አካል ውስጥ ነው።
የእንቅልፍ በሽታ ምታመጣው ትሪፓኖዞማ ተብላ ምትጠራ ጥገኛ ተውሳክ ራይቦዞም[2]
እነዚህ በሰንሰለት መልክ የተቀጣጠሉት ኑክሊዮታይዶች ከDNAው ይላቀቁና ከኑክሊየሱ ውጭ ወደሚገኘው የህዋሱ አካል ተጉዘው ራይቦዞም (Ribosome) የተባለ ረቂቅ በፐሮቲንና ኑክሌዪክ አሲድ የተሠራ አካል ዘንድ ይደርሳሉ። እዚህም እንድ ሌላ ትራንስፈር (Transfer) RNA የተባለ፣ አሁነም ኑክሌዪክ አሲድ በመቀጣጠል ከተሠራና፣ በአንድ ጎኑ አሚኖ አሲዱን ተሸክሞ ከመጣ ውህድ ጋር ይገናኛል ። ትራንስፈር RNA በሌላው ጎኑ ሶስቱን ኑክሊዮታይዶች የሚገጥሙ ኑክሊዮታይዶችን የያዘ ሲሆን፣ በራይቦዞሙ አማካኝነት ከDNAው ከመጣው RNA ጋር ተስተካክሎ እንዲያያዝ ይደረጋል። ብዚህ ዓይነት የRNA ሰንሰለቱን እየሳበና በዚያኛው ጎኑ ያሉትን አሚኖ አሲዶችንም እየቀጣጠለ፣ ይህን ሂደት በመደጋገም መጀመሪያ DNA ላይ በነበረው መረጃ መሠረት ፕሮቲኑ ይሠራል ማለት ነው። ይህ ፕሮትን የሚፈጽመው ተግባር ነው የዘረመሉን ባህርይ የሚያንጸባርቀው። ከታች የዮቲዩብ አገናኝ ላይ ያለው ተንቀሳቃሽ ምስል በቃል ከተጻፈው የተሻለ ዓይታ የሰጠናል ብዬ ገምታለሁ።
በ ራይቦዞም እና ትራንስፈር አር ኤን ኤ አማካይነት በመልዕክተኛው አር ኤን ኤ የሚገኘው መረጃ መሠረት ፕቶቲን ሲመረት
በዚ ጽሁፍ እንዴት ከDNA ተነስቶ ወደ ፕሮቲን፣ ቀጥሎም በዘር ወደሚተላለፈው ባህርይ እንደሚደረስ ለመግለጽ ያረኩት ሙከራ የሂደቱን አስደናቂነት ለአንባቢው ለማስተላለፍ የቻልኩ አልመስል አለኝ። በሌላ ልጥፍ ተመልሼ ከሌላ ጎኑ እንደገና እመለስበታለሁ። በሚቀጥሉት ልጥፎች አቶሞችን ተወት አርገን፣ ሌላው ተፈጥሮን ለመረዳት ወሳኝ የሆነውን ጨረርን እንዳስሳለን።
[1] https://microbenotes.com/characteristic-of-genetic-code
[2] https://doi.org/10.2210/pdb8OVE/pdbE, Rajan, K.S., Madmoni, H., Bashan, A. et al. A single pseudouridine on rRNA regulates ribosome structure and function in the mammalian parasite Trypanosoma brucei. Nat Commun 14, 7462 (2023). https://doi.org/10.1038/s41467-023-43263-6
