ገፆች

እሑድ 1 ማርች 2026

ረቂቁ አቶም ክፍል 5ሐ - አንድ ሰው ለመስራት የሚያስፈልገው መረጃ

ዲ ኤን ኤ (DNA) አራት የተለያዩ ኑክሊዮታይድ (Nucleotide) ተብልው የሚጠሩ ውህዶችን  በመቀጣጠል የተገነባ ትልቅ ውህድ እንደሆነ አይተናል። ስንቀጥልም፣ የተለያዩ ፍጡሮችን ስንመለከት፣ የነዚህ ኑክሊዮታይድ በዝት እና ቅደም ተከተል እንደሚለያይ መገንዘብ ተችሏል። ይሰው ልጅ ጂኖምም (genome, በጠቅላላ ያለን ዘረመል ስብስብ) 3.2 ቢሊየን  አካባቢ ኑክሊዮታይድ ያጠቃለለ ሲሆን፤ እንዚህም ወደ 20000 በሚጠጉ ዘረ መሎች ተዋቅሮ ይገኛል።  የዘረ መሎቹ መጠን በጣም የሚለያይ ሶሆን እያንዳንዱ ክ200 እስከ 2 ሚሊይን  ኑክሊዮታይድ ሊያካትት ይችላል።

በ2019 ቤእንግሊዝ ሃገር ማንቼስተር ሴንተር ፎር ጂኖሚክ ሜዲሲን (Manchester Center for Genomic Medicie) ተብሎ የሚጠራ ተቋም ሙሉ የሰው ልጅ ዲ ኤን ኤ ያካተተውን  3.2 ቢሊየን  ኑክሊዮታይድ ዝርዝር በ130 ጥርዞች 122976 የሚሆኑ ገጾችን በህትመት አስፍሮታል። 

የኑክሊዪታይድ ዝርዝርን የሚያሳይ ህትመት CC BY-SA 4.0

በሌላ ዓይነት ስንመለከተው ደግሞ፣ አነስተኛው የመረጃ መለኪያ ቢት (bit) ተብሎ የሚጠራውና፣ በዲጂታል ኮምፒዩተር ዘርፍም የምንጠቀምበት ሲሆን፣ ሁለት ብቻ ይዘት ሊኖረው ይችላል – ለምሳሌ ወይ 1 ወይ 0 መሆን ይችላል። ስለዚህም አራቱን ኑክሊዮታይድ ለመግለጽ ሁለት ቢት ተጠቅመን 00 ሲሆን ኤን (Adenine)፣ 01 ቲን (Thymine)፣ 10 ሲን (Cytosine)፣ እና 11 ጂን (Guanine)፣ አርገን መወከል እንችላለን። ብዚህ ዓይነት የ3.2 ቢሊየን ኑክሊዮታይድ መረጃ ለመያዝ 3.2 ሲባዛ በ 2 ማለትም 6.4  ቢሊየን ቢት ያስፈልገናል ማለት ነው። ይህም 800 መጋ ባይት (800MB) “ብቻ" ሲሆን በቀላሉ በአንድ ትንሽ  ፍላሽ ወይም ሞባል ስልክ ውስጥ መያዝ ይቻላል።

ስለዚህ አንድ ሰው ለመሥራት የሚያስፈልገንን መረጃ ወይም ንድፍ ማይት ችለናል። ችግሩ ግን ቋንቋውን ሙሉ በሙሉ ተረድትን፣ ለምንፈለገው ተግባር ለማዋል ገና አልበቃንም። ህትመቱ ላይ በዙ ፊደላት ተደርድረው እንመለከታለን፣ ለምሳሌ AACGTTACGTCGG... ግን ይህ እንዴት የአፍንጫችንን ቅርጽ እንደሚገልጽና፣ ሰልካካ እናርገው ብንል የኑክሊዮታይዶቹን አይነትና ቅደም ተከተልን ምን ማረግ እንዳለብን አናውቅም። መረጃው በነዚህ 3.2 ቢሊይን ኑክሊዮታይድ መሃል እንዳለ እናውቃለን - ቅርጹን ከወላጆቻችን ስለምንወርስ። ግን የትኞቹ ናቸው? ሙሉ በሙሉ ባይገባንም አንዳንድ ፍንጭ ተገኝቷል።

በሚቀጥልው ልጥፍ  ከተፈጥሮ ክስተቶች እጅግ አስደናቂ ከምንላችው አንዱ ወደሆነው የኑክሌዪክ አሲድና የፕሮቲን ተስስር ወየም ጥምረትን እንመለከታለን። 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ